>

" ቆራጣው ዮሀንስን" ፍለጋ (ቬሮኒካ መላኩ)

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ብዙ ነገሮች ተፈራርቀው አለፉ። 
 ምስኪኑ ጠቅላይ ሚ/ር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከስልጣኑ ተወገደ ወይም ራሱን አስወገደ ።
ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አርሲጣጢለስ፤ “የሰው ልጅ ፖለቲካዊ እንስሳ ነው” ብሎ ያኖረው ዘመን ተሻጋሪን ምልከታ እውን ይሆን ዘንድ “ፖለቲካ አልወድም ” ሲል የከረመው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስቴር በመተንበይና በጉዳዩ ላይ በመተንተን ተጠምዶ ከረመ ።
እርግጥ ስለመሪዎች ከዚህም የበለጠ መወራት አለበት የሚል እምነት አለኝ ። ግለሰብ መሪዎች  የአንድን አገር እጣፋንታና የሚሊዮኖችን እድል የመወሰን እድላቸው ከፍተኛ ነው። አፄ ሀይለስላሴ  ለአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ  እንደነገሩት ”  ህዝብ መምራት የበግ መንጋ አሰማርቶ እንደ መጠበቅ ቀላል አይደለም ።”   በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያውያን ” ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆን ?” እያሉ ቢብሰለሰሉ ትክክል ናቸው።
 የሮማን ኢምፓየርን ዋና ከተማ ሮምን እሳት ለኩሶ ከተማይቱን ስትጋይና አመድ ስትለብስ  እየሳቀ ሲዝናና የነበረው  ፣ በሮማ ኮሎስየም ህዝቦችን ለቀናት ለተራቡ አንበሳና ነብር ወርውሮ ከትዳር ጓደኛዋ ጋር ወይኑን እየተዝናና ይጎነጭ የነበረው ፣።  ” ምነው ይሄ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ አንድ አንገት በኖረውና በሰይፍ በቀላሁት ። ” እያለ የተመኘውና ሮምን የሽብርና የቅዤት ከተማ ያደረጋት ኔሮ  አንድ ግለሰብ ነበር።
ጀርመንን አዋህዶ ታላቅ  ያደረጋት ኦቶ ቫን ቢስማርክም ሆነ ጀርመንን ወደ የሰው ልጅ መታረጃ ቄራና ምድጃ የቀየራት ሂትለር  ሁለቱም ግለሰቦች ናቸው።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የነፃነት ጉልላትና  የአለም ጥቁር  ህዝቦች ምልክት ያደረጋት እምዬ ምኒልክም ሆነ ኢትዮጵያን ገነጣጥሎ የዜጎች መቀቀያ ድስት ያደረገው መለስ ዜናዊ አንድ ግለሰብ ናቸው።   ግለሰብ መሪዎች በአንድ አገርና ህዝብ እድል ላይ በአዎንታዊውም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ተፅእኗቸው ከፍተኛ ስለሆነ  በጉዳዩ ላይ መወያየቱ ትክክል ነው።
አሁን ወደ ተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ ስንመለስ ህውሃት ሀይለማሪያምን የሚተካ “ቆራጣው ዮሀንስን” ፍለጋ በር ዘግቶ እያሴረ ይመስላል። እዚህ ላይ ስለ 70 አመት አዛውንቱና እጄ ቆራጣው ዮሀንስ  ለማውራት ጊዜ ባይኖረኝም ቆራጣው ዮሀንስ ማለት  በ17ኛው ክዘ የሰሜን ጎርፍ አምጥቶ ጎንደር ላይ የጣለው ሚካኤል ስሁል የሚባል ወንበዴ  ከወህኒ አምባ  ደካሞችን እየመረጠ  ዙፋን ላይ ወዝፎ  እንደ አሻንጉሊት ከተጫወተባቸው ንጉሶች መካከል  የመጨረሻው ንጉስ ነበር።
በእኔ አመለካከት  የመጨረሻው ” ቆራጣው ዮሀንስ” ሀይለማሪያም ደሳለኝ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር ነገር ግን ደመቀ መኮንን ሽፈራው ሽጉጤና አቢይ አህመድ የሚባሉ ተራ ይዘው ተኮልኩለው እየጠበቁ ነው።
ሽፈራው ወይም ደመቀ መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን የሚይዙ ከሆነ የአቦይ ስብሃት የሽንት ጨርቅ ቀያሪ ከመሆን የዘለለ ሚና አይኖራቸውም ። በአቢይ አህመድም ቢሆን መተማመን ያስቸግራል።
እርግጥ የኦሮሞ አክቲቪስቶች አቢይ አህመድ የሚባል “ነቢይ ” እየመጣ እንደሆነ በመስበክ
ዳረጎቱን ህዝቡ አሜን ብሎ እንዲቀበል እውነታውን በማጥበረበር ወይም “ፎልስ ኮንሸስነስ” መፍጠር የፕሮፓጋንዳቸው ተቀዳሚ ሥራ ሆኗል።
ከነዚህ ሶስት ሰዎች የተሻለውን ለመምረጥ
በቅድሚያ በአገራችንን የናኘውን ውስብስብ ነባራዊ የፖለቲካ  ሁኔታ መመርመር  ያስፈልጋል። አሁንም ህውሃት የተባለው  ቡድን የሚናከስበት አብዛኛው ጥርሱ  ወላልቆ  በድዱ ቢቀርም አሁንም መከላከያና ደህንነት የሚባሉ ሁለት ጥርሶች ቀርተውታል ። ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር በህግ በተሰጠው ስልጣን ተጠቅሞ እነዚህን ሁለት ጥርሶች መንግሎ የሚጥል ከሆነ ታሪክ ይሰራል።
አሜሪካኖች እንደሚሉት ” ትላልቅ ችግሮች ታላላቅ መሪዎችን ይወልዳሉ ።” ።ሁለተኛው የአለም ጦርነት ዌንስተን ችርችልንና ሩዝቬልትን ወልዷል። በእኛም አገር ዘመነ መሳፍንት የሚባለው የችግርና የፈተና ወቅት  አፄ ቴዎድሮስን የሚያክል ታላቅ መሪ ወልዶልናል ።
ዛሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ችግር ውስጥ ነች ። ነገር ግን ዛሬም ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም ። ከወያኔ ውስጥ መሪ የሚሆን ቢጠፋም ከተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ታላላቅ መሪዎች ተፈጥረዋል። ኮለኔል ደመቀ ዘውዴ ፣ እስክንድር ነጋ ፣መረራ ጉዲና ፣  በቀለ ገርባ አንዱአለም አራጌ እና ሌሎችን ታላላቅ ሰዎች ወልዳለች።
አሁን በተጨባጭ እንደምንመለከተው  ወያኔ እንደ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የሚዘውረው ባለተራ ” ቆራጣው ዮሀንስ ” ከመፈለግ ለአንድትም ሰከንድ አያርፍም።።
ስሁል ሚካኤል በ17ኛው ክዘ እሱ ራሱ ንጉስ ሆኖ መግዛት ስለማይችልና የነጋሲነት ዘር  ስላልነበረው ደካሞችን አየፈለገ በእጅ አዙር  ለመግዛት ሞክሮ ነበር  ።
ዛሬም ህውሃት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ እንደማታገኝ ስታውቅ በእጅ አዙር “ጡል ጡል ” እያለ የሚላላካትን አሻንጉሊት  ጠቅላይ ሚኒስትር ፍለጋ ላይ ነች ።  ሽፈራውሽፈራው ሽጉጤ  በመላላክ ከሀይለማሪያም  ቢበልጥ እንጅ የሚያንስ አይደለም። ደመቀ መኮንንም  “የጎባጣ አሽከር ” የሚባለው አይነት ነው ። ብዙ ተስፋ የተጣለበት አቢይ አህመድ ነው ። አቢይንም ቢሆን ከጣሪያ በላይ የሚሰማው ያልተገራና ያልበሰለ የቄሮ ጫጫታ  አደንቁሮት ሊሆን ስለሚችል አስተማማኝ አይደለም ።  በዚህ ሁሉ ፍትጊያ ቀጣዩ ” ቆራጣው ዮሀንስ ” ማነው ካላችሁኝ ደመቀ መኮንን ይመስለኛል።የዚህን ግምታዊ ስሌት ለማወቅ በጣም ቀላል ነው። ህውሃት ከኦህደዱ እጩ  አቢይ አህመድ ይልቅ የብአዴኑን ደመቀን ይመርጣል ።  ሌላው ድርጅት ዴኢህዴን የህውሃት የጓሮ እርሻና የአትክልት ቦታ ስለሆነ በህውሃት የታዘዘውን መሪ እንድመርጥ ይደረጋል ። አቢይ  አህመድ የሚያገኘው ድምፅ የኦህዴድን እና ትንሽ የብአዴንን  እጆች ብቻ  ነው። በዚህ ስሌት መሰረት ቀጣዩ “ቆራጣው ዮሀንስ ” የገደል ስባሪ የሚያክለው ደመቀ መኮንን ይሆናል ማለት ነው።
 ለማንኛውም ለእኛ ኢትዮጵያውያን ሁነኛ መፍትሄው ሀይለማሪያም የተባለ ጉልቻ በአቢይ ወይም በደመቀ  መቀየር ሳይሆን  ስርነቀል ለውጥ ነው።  ማንኛውም  ስርዓት እንደ ሰው ይወለዳል፤ ያረጃል  ይሞታል ። ወያኔ ከማረጀትም አልፎ አርጧል ። ከዚህ በኋላ ወያኔ ላባውን በማራገፍ ንስር መሆን አይችልም። በዚህም መሰረት ከልሂቃኑ የሚጠበቀው ለውጡ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፤ ከለውጡ ቅኝት ጋር ተስማሚ የሚሆን አቋም በመያዝ፤ ለለውጥ ፈላጊው ህብረተሰብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ የሚመጥን ስርአት ይመጣ ዘንድ ትግሉን መቀጠል ብቻ ነው።
Filed in: Amharic