>
5:13 pm - Tuesday April 20, 5041

''ጀግንነት አይሰማኝም፤  ጀግና የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡'' (ወይዘሮ እማዋይሽ ዓለሙ)

የሐበሻ ወግ፡-  በቅድሚያ ከእስር በመፈታትዎ እንኳን ደስ አለዎ
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- አመሰግናለሁ፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ባልሳሳት እስር ቤት የቆዩት ዘጠኝ ዓመታት መሰለኝ
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- አዎ፤ ዘጠኝ ዓመት ጨርሼ አስረኛውን ዓመት የእስር ዘመን ልጀምር ስል ነው የተፈታሁት፡፡
የሐበሻ ወግ፡- እርስዎና አባሪዎችዎ የተከሰሳችሁትና የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባችሁ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብሎ ነው፡፡ እስቲ ወደ ኋላ ልመልስዎና በቁጥጥር ስር የዋሉ ቀን የነበረውን ሁኔታ ይንገሩኝ?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡-  እህ …. (ለአፍታ ከቆዘሙ በኋላ) አስታውሳለሁ ዕለቱ አርብ ቀን ነበረ፡፡ ሚያዝያ 16 ቀን 2001 ዓ.ም ከስዓት በኋላ ከቢሮ ወጥቼ ወደ ቤቴ ሄድኩ፡፡ ልክ ቤቴ ገብቼ አረፍ እንዳልኩ በርካታ ፌዴራል ፖሊሶች መሰስ ብለው ገቡና በቁጥጥር ስር ውለሻል፤ ቤትሽንም እንፈትሻለን አሉኝና የመያዣ ትዕዛዝ ወረቀት አሳዩኝ፡፡ ቤቴን የመመበርበሪያ ትዕዛዝ እንዲያሳዩኝ ጠየቅኩ፡፡ እሱንም አሳዩኝ፡፡ ከዛ ቤቱን መፈተሽ ጀመሩ፡፡ በቃ የቤቱን ዕቃ ሁሉ ምንቅርቅር አድርገው፣ ሹሮ እና በርበሬ እስኪቀላቀል ድረስ መፈተሽ ቀጠሉ፡፡ ቤተሰቦቼ የሚያደርጉትን ነገር እያዩ ያለቅሳሉ፡፡ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ፈተሹ፡፡
የሐበሻ ወግ፡- በብርበራ ወቅት ምን እንደሚፈልጉ ነግረውዎታል?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡-  የደበቅሽው የጦር መሣሪያ አለ ብለው ነው እንደዚያ ቤቱን ምንቅርቅር ሲያደርጉ ያመሹት፡፡
የሐበሻ ወግ፡- እሺ፤ ከዚያስ?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝ፡፡ እና  አንድ ክፍል አስገብተው ዘጉብኝ፡፡ ያን ቀን በሰላም አደርኩኝ፡፡ በበነጋታው ቅዳሜ ዐይኔን ሸፍነው ወደ ምርመራ ክፍል ወደዱኝ፡፡ ዐይኔ እንደተሸፈነ ጥያቄ ይጠይቁኝ ጀምር፡፡ ከዚህ በኋላ የሆነውን የምገልፅበት ቃል የለኝም፡፡ ….. እስካሁን ድረስ የሚዘገንነኝ የሚያወርዱብኝ አስፀያፊ ስድብ ነበር፡፡ ሴት ልጅ እንደዚያ ትሰደባለች እንዴ? ብቻ የማይሳደቡት ዓይነት አስፀያፊ ስድብ አልነበረም፡፡ መርማሪዎቹ… እየተቀባበሉ….. (ለሰከንድ ያህል ፀጥ ብለው) ድብደባቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ከ1 ወር በላይ “ምርመራ” የተባለው ዘለፋና ግርፊያቸው የቀጠለው፡፡ (በዚህች ቅፅበት ሁለት ሴቶች “እልልልልል” እያሉ ወደ ቤት ገቡ) በአጋጣሚ ይህቺ ልጅ (ወደ አንደኛዋ ሴት እየጠቆሙ) እዛው ማዕከላዊ ታስራ ነበር፡፡ በእኔ ላይ የተፈፀመውን ነገር እያየች በየቀኑ ታለቅስ ነበር፡፡ ደም ነው የሸናሁት! ደ……ም! …. እንዴት ሴት ልጅ ጡቷን ትገረፋለች? …… ጡቴ በድብደባ አብጦ ነበር፡፡  ብቻ ግን ….. የኢትዮጵያ ሕዝብ እግዜር ይስጠው የሃገር ውስጥ የውጭውም ሚዲያ ተጯጩሆ ከ1ወር በኋላ ሰኔ 1 ቀን ፍ/ቤት እንድንቀርብ ተደረገ፡፡ ያን ቀን ፍ/ቤት ተገኝታችሁ ከሆነ ያያችሁት ነገር ሊኖር ይችላል፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ካልተሳሳትኩ የእናንተ ክስ በአጭር ጊዜ ነው ውሳኔ ያገኘው …..
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- አዎ የፍርድ ሂደቱ እንደሌሎች ተከሳሾች አልተንዛዛም፡፡ ሰኔ አንድ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ፍ/ቤት ቀረብን፤ በዚያው ቃሊቲ ወረድን፡፡ ነሐሴ 13 ቀን ተፈረደብን፡፡ ከዚያ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ አልን፡፡ ጥቅምት 2 ቀን (2002) የይግባኛችንም ጉዳይ አበቃ፡፡ … እንዲያውም፤ የጡቴን መታመም ለጠ/ፍ/ቤት አመልክቼ ነው እንድታከም የታዘልልኝ፡፡ እንጂ ማዕከላዊም ሆነ ቃሊቲ በቂ ሕክምና ማግኘት አልቻልኩም ነበር፡፡ አንቲባዮቲክ እየሰጡኝ ነበር የሚሸኙኝ ….. ስቻ ያ ሁሉ መከራ አለፈ፡፡
የሐበሻ ወግ፡- በ2003 ዓ.ም ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙን ለመጠየቅ ቃሊቲ በመጣሁ ጊዜ አይቼዎት ነበር፡፡ ያን ቀን እርስዎን ከአጥር ወዲያ፣ ወላጅ እናትዎ እና ልጅዎ ናርዶስ ከአጥር ወዲህ ሆነው ሳያችሁ “ይህ ቤተሰብ የታሰረው ሶስት ትውልድ ተምሳሌት ነው” የሚል ስሜት ተሰምቶኝ ነበር፡፡ ለመሆኑ እናትዎ አሉ?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- አዎ አለች፡፡ በጣም ዕድለኛ ነኝ፤ አለች፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ማነው ስማቸው?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- እማሆይ ሙጭቴ ደምለው ትባላላች፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ዕድሜያቸው ስንት ይሆናል?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- 85 ዓመቷ ነው፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ከጎንደር እየመጡ ነበር የሚጠይቁዎት አይደል?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡-  አዎ፤ ለዘጠኝ ዓመታት ከጎንደር እየመጣች ነው የጠየቀችኝ፡፡ የታሰርኩ ሰሞን በየወሩ ነበር የምትመጣሁ፡፡ በኋላ አትምጪብኝ እያልኩ ስነጫነጭ በሁለት ወር አንዴ፤ ከዚያ በሶስት ወር አንዴ እየመጣች ትጠይቀኝ ገባች፡፡ በዚህ የእርጅና ዕድሜያ አገር አቆራርጣ መጥታ እዚህ ከደረሰች በኋላ በዋናው በር ገብታ እንድትጠይቀኝ ለማረሚያ ቤቱ አመልክቼ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል፤ ለ1 ጊዜ ብቻ ነበር የፈቀዱልኝ፡፡ ከዚያ በኋላ በታችኛው በር ግቢ ብለው ያባክኗት ገቡ፡፡ ብቻ እናት፣ እናት ናት፡፡ መተኪያ የሌላት፡፡ የእናቴ ነገር በጣም ያሳዝነኝ ነበር፡፡ ዘጠኝ ዓመት የታሰርኩት ብቻዬን አልነበረም፡፡ ከእናቴ ጋር ነው የታሰርኩት፡፡
የሐበሻ ወግ፡- እናትዎ በመጡ ጊዜ ምን ነበር የሚሉዎ?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- ሁሌም የምትለኝ አንድ ነገር ነው፤ “በርቺ” ነበር የምትለኝ፡፡ “እኔ ያለኝን ነገር ቆጣጥሬ የምመጣው አንቺ እንዳይርብሽ ነው፤ በህይወት እንድትኖሪልኝ ነው፤ በርቺ….” ነበር የምትለኝ፡፡በነገራችን ላይ – መጀመሪያ እኔን እንዲጠይቁኝ የተፈቀደላቸው እናቴ፣ ልጄ እና ባለቤቴ ብቻ ነበሩ፡፡ በኋላ ነው ሌላ ሰው እንዲጠይቀኝ የተፈቀደው፡፡ እና የእናቴ ቃል አንድ ብቻ ነበር፤ “በርቺ” የሚል፡፡
የሐበሻ ወግ፡- በአንድ ወቅት እርስዎና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ከሴት እስረኞች ተነጥላችሁ ለብቻ ለብቻ እንድትታሰሩ ተደርጎ እንደነበር መዘገቡን አስታውሳለሁ፡፡ በምን ምክንያት ነው?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- እ….. በለቅሶ ምክንያት ነው፡፡
የሐበሻ ወግ፡- የምን ለቅሶ?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- በጠ/ሚ/ር መለስ ሞት ምክንያት ግቢው ውስጥ ለቅሶ ነበር፡፡ መቼም ሰው ይሙት የሚል ሰው የለም፤ በእኛ መካከል ያለው የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ብቻ ነው፡፡ እንጂ ሁላችንም እህታማቾችና ወንድማማቾች ነን፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያኖች ነን፡፡ … እና ያኔ ግቢው ውስጥ የለቅሶ ሥነ ስርዓት ሲካሄድ እኔን ሰግደሻል፤ ርዕዮትን ስቀሻል ብለው ወደ ሌላ ቦታ ወስደው ለየብቻ አሰሩን፡፡ እኔ የዕድሜ ልክ ፍርደኛ ስለሆንኩ ወደዕድሜ ልክ ፍርደኛ ክፍል ወሰዱኝ፡፡ የዕድሜ ልክ ፍርደኞች ክፍል ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው መስኮቱ የተሰባበረ ስለሆነ በፍርገርጉ ብረት መሃል ሚገባው ብርድ ልዩ ነበር፡፡ እዚያ ውስጥ ነው እንድከርም ያደረጉኝ፡፡ እሷንም ሌላ ክፍል ነበር እንድትከርም ያደረጓት፡፡
የሐበሻ ወግ፡-  እንግዲህ ያ ሁሉ ተግዳሮት አልፎ  ከእስር ተፈተዋል፡፡ የዕድሜ ልክ ፍርደኝነትዎም አብቅቷል፡፡ እዚያ ሆነው ይኼ ነገር እንደሚሆን ወይም እንደሚመጣ ገምተው ነበር?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- እንግዲህ ከእግዚአብሔር በታች ያለው ሕዝብ ነው፡፡ አንድ ቀን፣ ህዝብ ብሶቱ ሲበዛ እኛ ብቻ ሳንሆን እስረኞች በሙሉ የሚፈቱበት ቀን ይመጣ ይሆናል ብዬ እገምት ነበር፡፡ እስር ቤት ውስጥ የሚሆነውና የምታየው ሁሉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዜጎች እስር ቤት ሆናለች፡፡ ወጣት ሆነው ገብተው እዛው ያረጁ እስረኞች አለ፡፡ እናም ህዝብ አንድ ቀን አሸንፎ እኛም እንፈታለን ብዬ እገምት ነበር፡፡ ግን እንዲህ በቅርብ ጊዜ ወይም አሁን ይሆናል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡
የሐበሻ ወግ፡- በነገራችን ላይ ከእስር ለመፈታት ዕቃዎትን ይዘው ከወጡ በኋላ “አልፈታም” ብለው ተመልሰው ነበር፡፡ ለምንድነው?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- ያን ቀን ቀስ ብለው መጥተው እኔን “ዕቃሽን ይዘሽ ውጪ” አሉኝ፡፡ ይዤ ወጣሁ፡፡ ሌሎቹስ ስል ይመጣሉ ይሉኛል፤ እንደገና ደጋግሜ ሌሎቹስ ስል “ስለሌሎቹ አንቺ ምን አገባሽ” አሉኝ፡፡
የሐበሻ ወግ፡-  “ሌሉቹስ” ብለው የሚጠይቁት ከእርስዎ ጋር በአባሪነት የተከሰሱትን የኢህአዴግ ጄኔራሎችን ነው?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- አይደለም፤ ሌሎች በርካታ ሴት እስረኞች ነበሩ፡፡ ትፈታላችሁ ተብለው ዕቃቸውን የላኩ ነበሩ፡፡ ከተለያየ ክልል የመጡ ናቸው፡፡ …. በዚህ መሃል ከአርባምንጭ የታሰረችው አየለች አበበ ከኦሮሚያ ክልል የታሰረች ባጩ መርጋ መጡ፡፡ ሌሎቹ ግን አልመጡም፡፡ በዚህ ጊዜ እኔም አልፈታም አልኩ፡፡ “በቃ ተውአት” አሉና ወደ እስር ቤት ተመለስኩ፡፡ ቢያመናጭቁኝ ምን ቢሉኝ ፍንክች የማልል ስሆን ዝም አሉኝ፡፡ ይህ በሆነ በሶስተኛው ቀን “ሌሎችስ” ብዬ መፈታታቸውን የጠየቅኳቸው ልጆች ተፈቱ፡፡ እነሱ ደግሞ በተራቸው እማዋይሽስ ብሉው ሲጠይቁ “እዛው ትበሰብሳለች፤ አትወጣም” ተባሉ፡፡ … የሆነ ሆኖ እግዚአብሔር ቀድሞ ቀንበሩን ሰብሮታልና እኔም ወጣሁ፡፡ እኔም ዕቃዬም እየተጎተትን ነው የወጣነው፡፡ ሻንጣዬን ብታየው ሲጎትቱት ስብርብር ብሏል፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ በውጪ ያለውን መንፈስ ሲያዩት ምን ተሰማዎት?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- ሁለት ዓይነት ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አንድነት በመምጣቱ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ በፊትም የምለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው፤ ነው፡፡ በሌላ በኩል የምሰማው አንዳንድ ወሬ አላስደሰተኝም፡፡ እርግጥ ነው ትግል ያስፈልጋል፡፡ ትግሉ እንዳለ ሆኖ በብሔር ልዩነት የተነሳ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ እንደዚያ ማድረግ “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” ዓይነት ነው፡፡ እንደነገርኩህ፤ እኔ የምለውም የማምነው እኛ አንድ ነን ብዬ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያኖች ሰርገኛ ጤፍ ማለት ነን፡፡ የተቀየጥን፤ የማንለያይ፡፡ ስለዚህ አንድነታችንን ማጠናከር ነው ያለብን፡፡ እንግዲህ እነሱም ….ጥፋታቸውን እያመኑ ነው፡፡ ጥፋት አጥፍቻለሁ የሚል ሰው ደግሞ እዛው ወንበር ላይ ተቀምጦ አይደለም እንደዛ ማለት ያለበት፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መውሰድ የሚገባቸው እርምጃ አለ፡፡ እንግዲህ እነሱንም ልቦና ይስጣቸው ነው የምለው፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ለዘጠኝ ዓመታት ብዙ መከራ አልፈዋል፤ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ይህን መስዋዕትነት በመክፈልዎ ጀግንነት ይሰማዎታል?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡-  በፍፁም፤ ጀግንነት አይሰማኝም፡፡ ጀግና የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው በመከራ በብዙ ውስጥ አልፎ፤ ከዚያም ወደ አንድነት መጥቶ ለዚህ ውጤት የበቃው እኛም የተፈታነው፡፡
የሐበሻ ወግ፡-  መልካም፤ እርስዎን ለማግኘት ወደዚህ ስንመጣ ስልክ ደውለንልዎት በስልክ የቤትዎን አድራሻ እየጠቆሙን ነበር፡፡ እርስዎ ግን ቤትዎ አልነበሩም፤ ጥቂት ደቂቃዎች አስጠብቀውናል (ሳቅ) የት ሄደው ነው?
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- ቅድም ጠቆም አድርጌህ ነበር፡፡ እዚህ ቤቴን ሳላደራጅ ወደ ጎንደር መሄድ ወስኛለሁ፡፡ በተለይ 9 ዓመት ሙሉ “ከእኔ ጋር የታሰረችው” እናቴን ለማየት ቸኩያለሁ፡፡ ወደዚያ ለመሄድ ደግሞ መፈቻ ወረቀት ብቻ በቂ አይለም፡፡ እኔነቴን የሚገልፅ ፎቶ ያለበት (መታወቂያ) ነገር መያዝ ያስፈልግሻል አሉኝ፡፡ እና የባንክ ደብተር ነበረኝ፤ እሱን ካለበት ለማምጣት ሄጄ ነው ከቤት ያጣችሁኝ፡፡
የሐበሻ ወግ፡- እንደዛ ከሆነ “መልካም መንገድ” ብዬ ልሰናበትዎታ…
ወ/ሮ እማዋይሽ፡- አሜን
                            ***      ***     ***
ከወ/ሮ እማዋይሽ ጋር እንዲህ ባለ መልኩ ተወያይተን እንዳበቃን፣ ሌላዋ ተፈቺ እስረኛ ወጣት ኢየሩሳሌም ተስፋው 3 ሴቶች አስከትላ ወዳለንበት ሳሎን ገባች፡፡ ያስከተለቻቸው 3ቱም ሴቶች ሂጃብ ለብሰዋል፡፡ ከወ/ሮ እማዋይሽ ጋር ተሳሳሙ፡፡ “እሷም ባለፈው መስከረም ወር ነው ከእስር ቤት የተፈታችው” አሉን ወ/ሮ እማዋይሽ፡፡ እናም ከሙስሊሟ ወጣት እና ከኢየሩሳሌ አጠር ያለ ቆይታ ለማድረግ ወሰንን።
Filed in: Amharic