>

ጉርምስና ያሸነፋት ሃገር (ተሾመ ታደሰ)

የፖለቲካ ጉርመስና የዕድሜ ድንበር የለውም፡፡ ሰማኒያ ዓመት ሞልቶህም አንደ አፍላነትህ ዘመን ዘራፍ ያሰኝሀል፡፡ ለገላጋይ አስቸግረህ መደራደር ውርደት ይመስለሃል፡፡ ወዳጄ በሃይሉ ሚደቅሳ እዚህው ገፅ ላይ እንደተረከው ሰጥቶ መቀበል ነውር መስሎህ ያንዘረዝረሐል፡፡

ሰው እንደኔ የማያስበው ማን ስለሆነ ነው ብለህ ያንገበግብሀል፡፡ አካልህ ቢያረጅ እንኳን ከውስጥህ ያለው ጎረምሳ የፖለቲካ አመልህ ግደለው ግደለው ይልሃል፡፡ (እባክዎ እነዚህ ምልክቶች በአስተሳሰበዎ ላይ ሲሰተዋሉ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ይሂዱ ) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥንትም ዛሬም የጎረምሶች መጫወቻ ነው፡፡

መስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) እንዘጭ እንቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ! በተባለ መፅሐፋቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግሩ በጎረምሶች ዕጅ መውደቁ ነው ይላሉ፡፡

በዚች ሀገር 26 ዓመት ስልጣን ላይ ተኑሮም ጭምት ባለስልጣን ማግኘት ብርቅ ነው፡፡ አሁንም ከጫካ አስተሳሰቡ ያልወጣ አፈለኛ የፖለቲካ ስሜቱ ያልበረደለት አረጋዊ ማግኘት በኢህአዴግ ቤት የተለመደ ነው፡፡ ስልጣን ሊያካፍለህ አይደለም እስኪ አስነካኝ ብተለው የሚገድልህ ብዙ ነው፡፡

ደግሞም እነሱ ማን ሁነው ነው የእኛን ትግል ነጥቀው ቤተ መንግስት የገቡት በሚል ብስጭት ፊቱን እየነጨ ኑ እናምፅ የሚል አዛውንትም በባህር ማዶ በሽ ነው፡፡ ፕ/ር መስፍን ከላይ በጠቀስኩት መፅሃፈቸው የጎረምሳ ፖለቲካችን ጅማሮ ከየካቲቱ አብዮት እንደሚነሳ አድረገው ፅፈውታል፡፡

ለእኔ ግን የጎረምሳ ፖለቲካ ዘመኑ ዕሩቅ ነው፡፡ ስልጣን በዘር በሚተላለፍበት የሰለሞናዊም ሆነ ዛግዌ ስሮ መንግስት ውስጥ ብዙ የፖለቲካ ጎረምሶች ይችን ሀገር አስተዳድረዋል፡፡ ወደ መካከለኛው ዘመን ብንመጣ እንኳን አፄ ሱስንዮስ አፍላ ዕድሜያቸው ከአፍላ ፖለቲካቸው ጋር ተዳምሮ አዕላፍ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሐይማኖት ተከታዮችን አስቀልቷል፡፡

ከዚህ ዘመን በኃላ የመጣው ልጅ እያሱም በዕድሜው ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውም ጎረምሳ ነበር፡፡ ንግስት ዘውዲቱም ሆነ ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ጉርምሰና ያሸነፋቸው በተፈጥሮያዊው ዕድሜያቸው ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውም ጭምር ነው፡፡

ታሪካዊ የሆነችው የየካቲት ወቅት ግን የዘመናዊው ፖለቲካችን ጎረምሶች ማምረቻ ወቅት ተደርጋ የምትወሰድ ናት፡፡ ሶሻሊዝም በሚሉት ምንትስ (መንፈስም ይመስለኛል ) ተለክፈው በየፊናቸው ተዋድቀዋል፡፡ አንድ ሀገር እያላቸው መደማመጥ ተስኗቸው የዕድሜ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ጉርምስናቸውም ተጭኗቸው እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ተጫርሰዋል ፡፡

ሌላው የጎረምሳ ስብስብ ደርግም ነገሩን በብልሀት መፍታት አቅቶት አዕላፍ ጎረምሶችን ጨረሳቸው፡፡ በዚህ ተስፋ የቆረጡት ብዙ ወጣቶችም ሀገር ለቀው ተሰደዱ፡፡

ከዚህ በተቃራኒው የደርግ አካሄድ እንደማያዋጣ ቀድመው የተረዱ ወጣቶች ጫካ ገብተው ብረት አነሱ፡፡ የደርግ ሰዎች ተፍጥሯዊ ዕድሜያቸው ቢጃጅም የፖለቲካ ጉርምስናቸው ግን ባላበት አዕላፍ ዘመናትን ተሸግሮ ከመደማመጥ ይልቅ በአፈለኝነት ስሜት ነገሮችን እየፈቱ ተጓዙ፡፡

ይህ አፍለኝነት በሌላ ጎረምሳ ተገታ፡፡ ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ በአፍላ ወጣቶች እየተመራ ምኒልክ ቤተመንግስት ገባ፡፡ እሱም በተራው እንደትናንቱ ሁሉ በጉርምስና አመሉ ቀጠለበት፡፡ ከእኔ የተለየ ጠላቴ ነው በሚል የሰፈር ፀብ ማስነሳት ጀመረ፡፡ በጉርምስና ፖለቲካ ክፉ ያሰበብትን ሁሉ አስተንፍስለሃለሁ እያለ ዛተ፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት አርባ ዓመታቸውንም ተሸግረው ከፖለቲካ ጉርምስና አመላቸው አልተላቀቁም፡፡ ዕድሜያቸው 60 ሞልቶም ይኼው አመላቸው አብሯቸው አለ፡፡

የተቃዋሚ መሪዎችም ዕድሜያቸው የቱንም ያህል ቢሆን የፖለቲካ ጎረምሳ ናቸው፡፡ ዘመናቸው ሀምሳም ይሁን ሰባ ዛሬም ከእፍላነታቸው ዕልክ ጋር ይጓዛሉ፡፡ የአልሸነፍ ባይነት የጎረምሳ ፖለቲካ አመላቸው አንገታቸው ስር ዕየተናነቃቸው በማህበራዊ ድረ-ገፆች ሂድና ግደለው ፣ደምስሰው ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያዊ ባህል መሰረት በዚህ እድሜያቸው ሀገር እንደመሸምገል የፖለቲካ ጉርምስና ፈንቅሏቸው ሰለበቀለኝነት ይሰብካሉ፡፡

ለዛሬው ፖለቲካችን መሰረታዊው መነሾ ይኼው የጉርምስና ፖለቲካ ነው ፡፡ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ያሉ ዋናዎቹ መሪዎች በተፈጥሯዊ ዕድሜያቸው ወጣትነትን ቢሻገሩም ዛሬም ለፖለቲካችን ጎረምሳ ናቸው፡፡ ሂድ ግደለው ፣እሰረው እያሉ ከእድሜያቸው በታች ይጫወታሉ ፡፡

ፍፁማዊ መጠላላትን እንደ በጎ ልማድ ለዚህ ትውልድ ያወርሳሉ፡፡ በጠላት መቃብር ላይ ካልሆነ የሀገር ስርየት የለም እያሉ ይሰብካሉ፡፡ በመንፈስ ጉርምስናቸውን ሙጥኝ ያሉ አዛውንትና አረጋውዊ ፖለቲከኞች በተፈጥሮ ጎረምሳ ለሆኑት የእኔ ዘመን ልጆች ጥላቻን ይሰብካሉ፡፡ የነገዋንም ሀገሬን ያፈርሳሉ ፡፡

Filed in: Amharic